Sunday, June 02, 2013

ሰማያዊ ፓርቲ የተቃውሞ ሰልፍ አካሄደ

(June 02, 2013, (አዲስ አበባ))--ሰማያዊ ፓርቲ የጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ግንቦት 25/ 2005 ዓ/ም በአዲስ አበባ ተካሄደ፡፡መንግስት በበኩሉ ሰልፈኞቹ ያቀረቡት ጥያቄ የህግ ስርአቱን መሰረት ያልጠበቀ ነው ብሏል፡፡ ፓርቲው ለተቃውሞ ሰልፍ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን የጠራው አራት ጥያቄዎችን በማንሳት መሆኑን የሰልፉ አስተባባሪዎች በሰልፉ ወቅት ተናግረዋል፡፡

በአሸባሪነት ተጠርጥረው የተያዙ ግለሰቦች ይፈቱ፣ የኑሮ ውድነት የሚቀረፍበት ፖሊሲ ይቀረፅ፣ ተዘዋውሮ የመስራት ነፃነት ይከበርና ህገ መንግስቱን የሚቃረኑ አፋኝ አዋጆች ይሰረዙ የሚሉ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ሰልፈኞቹ በፅህፋቸውና በቃል ባሰሟቸው መፈክሮች በስፋት የተንፀባረቀው “የሙስሊሞች የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ” ብለው የሚጠሯቸውና ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ተይዞ ያሉ ተጠርጣሪዎች ይፈቱ የሚል ነበር፡፡



ከዚህ በተጨማሪ ሰልፈኞቹ በኢፌዲሪ ህገ መንግስት እውቅና የተሰጠው ሰንደቅአላማ የኛ አይደለም በማለት እንዳይታይ ሲከላከሉ ነበር፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት መንግስት ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

ሰማያዊ ፓርቲ  በጠራው ሰልፍ የተንፀባረቁት መፈክሮችና ቅሬታዎች ህገ መንግስቱ በፖለቲካና በሃይማኖት መካከል ያስቀመጣቸውን የልዩነት መስመር የጣሱ ናቸው ሲሉ የመንግስት ኮሚሊኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ ሽመልስ ከማል ገልፀዋል፡፡

የሰልፉ ተሳታፊዎች በሽብርተኝነት ተጠርጥረው የተያዙና ጉዳያቸው በፍርድ ቤት  እየታየ ያሉ ግለሰቦች  ይፈቱልን ብለው ያቀረቡት ጥያቄ የህግ ስርአቱን መሰረት ያልጠበቀ ነው ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው ፡፡ 
ምንጭ፡ ኢሬቴድ
Home 

No comments:

Post a Comment